የጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል ያለመ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤናው ሴክተር የመንግሥት እና የግሉን ዘርፍ ቅንጅት አጠናክሮ የጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል ያለመ ውይይት ተካሄዷል፡፡
በውይይቱ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ፣ የኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን አመራሮች እንዲሁም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ በጤናው ሴክተር የመንግስትንና የግሉ ዘርፍን ቅንጅት በሚያጠናክሩ በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በጤናው ሴክተር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማጠናከር፣ የሕክምና ግብዓት እጥረቶችን ከሟሟላትና ሌሎች ተግዳሮቶችን በቅንጅት ከመፍታት አኳያ፣ ከጤና ተቋማት ፍቃድና ቁጥጥር እንዲሁም የእውቅና አሰጣጥን በተመለከት በጋራ መስራት በሚቻልበት ላይ ውይይት ተካሂዷል።
ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት÷ የግል ጤና ዘርፍ የጤና ስርዓቱን ለማጠናከር ባለው እንቅስቃሴ መልካም ቢሆንም ከተቀመጡ ግቦች አኳያ ግን ይበልጥ መጠናከርና ወደ ላቀ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
በጋራ የሚሰራበት ጠንካራ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑንና በሚቻለው አቅም ለግል ዘርፉ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡