ለምን ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ አለብዎ?
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓመታዊ የጤና ምርመራ በተለያየ የዕድሜ ክልል ላይ ላሉ ሰዎች የሚደረግ እና ለአንድ በሽታ የመጋለጥ ዕድልን ቀድሞ ለማወቅ የሚያስችል የምርመራ ዘዴ ነው።
እድሜ እና ፃታን መሠረት አድርገው በየአመቱ እና ከዛም በላይ ሊደረጉ የሚገቡ የምርመራ ዓይነቶች አሉ።
እነዚህን ምርመራዎች መረዳት እና መቼ መጠየቅ እንዳለብዎት ማወቅ ጤናማ ሆነው እንዲቆዩ እንደሚያግዝ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ለምን ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ አለብዎ?
• በየጊዜው የሕክምና ምርመራ ማድረግ በህመም የመጠቃት እድልዎን ይቀንሳል፡- መደበኛ የሕክምና ምርመራዎች ሰውነትዎ እና አእምሮዎ ጤናማ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይረዳል።
እንደ ካንሰር፣ የልብ ህመም፣ ስትሮክ፣ የኩላሊት ህመም፣ የስኳር ህመም፣ የደም ግፊት መጨመር እና አንዳንድ በቅድመ ጥንቃቄ ሊከላከሏቸው የሚችሏቸውን ህመሞች ለመቆጣጠር ቀደም ብሎ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።
• መደበኛ ምርመራዎች ከውጥረት ጋር የተያያዙ በሽታዎችን ለመለየት ይረዳሉ፡- መደበኛ ሙሉ የሰውነት ምርመራ ከውጥረት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዲመረምር እና የሚያስፈልግዎን ህክምና በጊዜው እንዲያደርጉ ያግዛል፡፡
• ዓመታዊ ምርመራዎች የደም ምርመራ ውጤቶችን ለመለየት ይረዳሉ፡- ብዙ ሰዎች እንደ ጉንፋን ወይም ትኩሳት ያሉ የተለመዱ በሽታዎች ምልክቶችን በቀላሉ ይረዳሉ ምክንያቱም እነዚህ ምልክቶች በአካል ላይ የህመም ስሜትን ስለሚፈጥሩ ነው፡፡
ሆኖም በጊዜው በቂ ህክምና ካላደረጉ የበሽታውን ምክንያት መለየት የማይቻል ሊሆን ይችላል፡፡ለዚህም ነው የህክምና ባለሙያዎቸ ወደ የህክምና ስፍራ ሲሄዱ በቅድሚያ የደም ምርመራ የሚጠየቁት፡፡
በዚህም የደም ምርመራዎች የተለያዩ በሽታዎችን ለማወቅ እንደሚረዱ ይነገራል፡፡
• ወቅታዊ የጤና ምርመራዎች ማድረግ ስለ ጤንነትዎ የበለጠ እንዲያውቁ ያደርግዎታል፡- ብዙዎች የህክምና ተቋማትን የሚጎበኙት ሲታመሙ እንጂ ቀድመው ያሉበትን የጤና ሁኔታ ለማወቅ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
መደበኛ የጤና ምርመራ ማድረግ ስለጤንነትዎ በመረዳት ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለመምራት ያስችልዎታል፡፡
• ዓመታዊ ሙሉ የጤና ምርመራ የጤና እንክብካቤ ወጪዎችን እንዲቀንሱ ያግዝዎታል፡- በየጊዜው የሚደረግ ምርመራ በሽታን ለመከላከል እንዲሁም ሌሎች በሽታዎችን ገና በለጋ ደረጃ ለማከም ይረዳል።
ይህ ደግሞ የመታመም እድልዎን በማሳነስ የህክምና ወጪዎን እንደሚቀንስ ከስዋኮን ኢንተርናሽናል ሆስፒታል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።