በቤቶች ግንባታ ዘርፍ ከተሰማሩ የጣሊያን ኩባንያዎች ጋር ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል በጣሊያን፣ ሮምና ሚላን ከሚኖሩ ዳያስፖራዎችና በቤቶች ግንባታ ዘርፍ ከተሰማሩ የጣሊያን ኩባንያዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ ረሻድ ከማል÷ ከኢትዮጵያዊያንና ትውልድ-ኢትዮጵያዊያን ጋር በነበራቸው ውይይት ኮርፖሬሽኑን ከኋላ ቀር አሰራር እንዲሁም ከተመሳሳይ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች መላቀቁን አብራርተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአጭር ጊዜና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የቤት ግንባታ ልምድ ማዳበሩን ጠቅሰው፤ እያደገ ያለውን የዜጎችን የቤት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የቤት ግንባታ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ያማከለ የቤት ግንባታ ለማስጀመር የህግ-ማዕቀፍ፣ የዲዛይን፣ ከቁጠባና የብድር አገልግሎቶችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የተገናኙ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ገልፀዋል።
በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ አምቢሳ÷ ኮርፖሬሽኑ ዳያስፖራውን የሚያሳተፍ ፕሮጀክት ለመጀመር መዘጋጀቱ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ጋር በልማት እንዲተሳሰሩ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው÷ በኮርፖሬሽኑ እየተመዘገበ ባለው ለውጥ መደሰታቸውን ገልፀው፤ በቤት ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ ዝግጁነታቸውን ማረጋገጣቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ የተመራው ልኡክ በጣሊያን ቤቶች ግንባታ ልምድ ካካበቱ ኩባንዎች ጋር አብሮ ለመስራት መግባባት ላይ የደረሱ ሲሆን÷ ኩባንያዎችንም ጎብኝተዋል።