በጎፋ ዞን በተከሰተ የመሬት ናዳ ከ20 በላይ ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ዛሬ ረፋድ 4 ሠዓት አካባቢ በተከሰተ የመሬት ናዳ አደጋ ከ20 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
በተከሰተው አደጋ እስካሁን በተደረገ ፍለጋ ከ20 በላይ አስከሬን መገኘቱንና የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ምስክር ምትኩ ተናግረዋል፡፡
ለነፍስ አድን ተግባር በስፍራው የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የአካባቢው ነዋሪዎችም የአደጋው ሰለባ ሆነዋል ማለታቸውን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል፡፡
የአስክሬን ፍለጋና የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም አመላክተዋል፡፡