አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አመራሮችና ሠራተኞች አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኖሩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህና የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት አመራሮችና ሠራተኞች በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸው አኖሩ፡፡
አቶ አደም ፋራህ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፥ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የትናንት፣ የዛሬና የነገን ትውልድ የሚያስተሳስርና ኢትዮጵያ ምቹ ፕላኔት የመፍጠር ሚናዋን እየተወጣችበት የሚገኝ ግዙፍ ኢኒሼቲቭ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ትናንት የተሠሩ ታሪኮችን ለማስቀጠል፣ አደጋዎችን በዘላቂነት ለመከላከል፣ መልክዓ-ምድራችንን ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመጠበቅ የሚያስችል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ለዛሬው ትውልድም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳካት ጉልህ አበርክቶ እንዳለውም አንስተዋል።
በመሆኑም የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ በገጠርም ሆነ በከተማ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በመግለጽ፤ ብልጽግና ፓርቲ ለመርሐ-ግብሩ መሳካት የመሪነት ሚናውን እየተወጣ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።