የሶማሌና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 6ኛ የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬ መካሄድ የጀመረ ሲሆን በጉባዔው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ የክልሉን የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ዋና ኦዲት ቢሮ ዓመታዊ የስራ እንቅስቃሴ ለጉባዔው ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል።
ምክር ቤቱ በቆይታው የክልሉን የ2017 በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ እና በጀት እንደሚያፅድቅም ይጠበቃል።
በተመሳሳይ 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ የጀመረው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት፤ በ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም የክልሉ መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የበጀት ማከፋፈያ ቀመር እና የ2017 በጀት ዓመት የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ እንደሚያፀድቅም ይጠበቃል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
ምክር ቤቱ የተለያዩ ክልላዊ ተቋማትን የ2016 በጀት ዓመት ስራ አፈፃፀም ሪፖርት የማድመጥ እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅዶች ላይ መወያየት ከምክር ቤቱ ውሎ አጀንዳዎች መካከል ናቸው ተብሏል።