ለመዲናዋ ንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት እየተዘረጋ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአዲስ አበባ ከተማ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለሚያቀርበው የለገጣፎ ለገዳዲ የውሃ ፕሮጀክት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርጋታው ከፍተኛ ጥራት ባላቸው ግብዓቶች የሚከናወን በመሆኑ ከዚህ በፊት የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ነው ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ ግፊት የሚደርጉና የሚያጣሩ በአጠቃላይ 25 አዲስ ጉድጓዶችን የያዘ ሲሆን÷ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 9 ነጥብ 6 ሜጋ ዋት ሃይል በቀን እንደሚጠቀም ተገልጿል፡፡
ይህም በውሃ ተጠቃሚ ብዛት ሲቀየር በቀን 860 ሺህ ሰዎችን ውሃ እንዲያገኙ እንደሚያስችል ነው የተገለጸው፡፡
ለፕሮጀክቱ 81 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ባለ 33 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ ሃይል ተሸካሚ መስመር እንደሚያስፈልግ የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
እስካሁን 79 ኪሎ ሜትር ያህሉ የተዘረጋ ሲሆን÷ 18 የተለያየ አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች እና 1 ሺህ 688 ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የኮንክሪት ምሰሶዎች መተከላቸው ተጠቁሟል፡፡
በአሁን ሰዓት ለ16 የውሃ ጉድጓዶች የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሥራው ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው እና ቀሪ ሥራዎች በጥቂት ጊዜ እንደሚጠናቀቁም ተገልጿል፡፡