Fana: At a Speed of Life!

የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግና ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች በደብረ ብርሃን አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ እና የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በደብረ ብርሃን ከተማ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አከናውኗል።

በብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ዋና ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ወጣት ሰብለ በቀለ በወቅቱ እንደገለፀችው÷ መንግስት የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።

የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም የተጀመሩ የልማትና የሰላም ስራዎች ላይ ተግቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝባለች።

ለዘላቂ ሰላም መስፈን የውይይትና የምክክር ባህልን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግራ፤ በተያዘው የክረምት ወራት በመላ ሀገሪቱ በርካታ የሊጉ አባላት ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑን ነው የገለጸችው፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ወጣቶች ሊግ ሃላፊ ወጣት ተስፋሁን ተሰማ በበኩሉ÷ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንድነትን በማጠናከር ሁለተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያግዛል ብሏል።

በተያዘው ክረምት በክልሉ አባላትን በማስተባበር ችግኞችን በመትከል የአረጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን የመደገፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም 3 ሺህ የአረጋዊያንን መኖሪያ ቤቶችን ጥገናና 1 ሺህ ቤቶች ደግሞ በአዲስ ለመስራት እንዲሁም 4 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የተራቆቱ መሬቶችን አረንጓዴ ለማልበስ የችግኝ ተከላ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ ነው ያሉት ደግሞ የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ናቸው።

ከወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ተማሪ ሀይሌ ጋጭቶ በበኩሉ÷ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፥ ስራን ከመልመድ ባሻገር ማህበራዊ መስተጋበሮችን እንድንወራረስ አግዞናል ብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.