ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናኑ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናንተዋል፡፡
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አመራሮች በተጨማሪ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና የወላይታ ዞን አስተዳደር የአመራር አካላት በአደጋው የተጎዱ ወገኖችና ቤተሰቦቻቸውን በስፍራው በመገኘት አጽናንተዋል፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ÷ በተከሰተው አደጋ በራሳቸው እና በክልሉ ህዝብ ስም የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው ቤተሰቦቻቸውን በአደጋው ላጡ ወገኖች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በጥሬ ገንዘብ 5 ሚሊየን ብር እንዲሁም በዓይነት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
የጎፋ ዞን አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር) በዞኑ የተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ እጅግ ዘግናኝ መሆኑን ተናግረው የተከሰተው አደጋ ከዞኑ አቅም በላይ በመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ በስፍራው ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ያጽናኑት የወላይታ ዞን አስተዳደር አቶ ሳሙኤል ፎላ÷ በተከሰተው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
ዞኑ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ በቀጣይም የሚያስፈልገው ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በማቱሣላ ማቴዎስና መለስ ታደለ