አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዳይጠቀሙ አገደች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዳይጠቀሙ የሚያግደውን ህግ በፓርላማ አፅድቃለች፡፡
በውሳኔው መሰረትም በሀገሪቱ እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች የቲክቶክ፣ ስናፕ ቻት፣ ፌስቡክ፣ ሬዲት፣ ትዊተር (ኤክስ) እና ኢንስታግራም አካውንት መክፈት አይችሉም፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የማህበራዊ ትስስር ገፆች ታዳጊዎች አካውንት እንዲከፍቱ የሚፈቅዱ ከሆኑ 50 ሚሊየን የአውስትራሊያ ዶላር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው መንግስት አስጠንቅቋል።
የአውስትራሊያ መንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ሚሸል ሮውላንድ÷ በሀገሪቱ ሰፊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ድጋፍ ያገኘው ይህ ውሳኔ የታዳጊዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአውስትራሊያ እድሜያቸው ከ14 እስከ 17 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች ጎጂ ይዘት ያላቸውን ጉዳዮች በማህበራዊ ትስስር ገፆች ሲመለከቱ እንደነበር አስታውሰው÷ ክልከላው ታዳጊዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚደርስባቸውን ጫና ይቀንሳል ብለዋል፡፡
ከአውስትራሊያ አስቀድማ ስፔን ባለፈው ሰኔ ወር ከ14 እስከ 16 ዓመት ያሉ ታዳጊዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዳይጠቀሙ መከልከሏ ይታወቃል።
በአሜሪካም በተወሰኑ ግዛቶች ላይ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል መባሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡