በኦሮሚያ ክልል 8 ሺህ 843 መኖሪያ ቤቶች ለመምህራን ተሰጡ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017(ኤ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች 8 ሺህ 843 መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለመምህራን መሰጠታቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የእቅድና በጀት ዝግጅት ዳይሬክተር ሃሰን እንድሪስ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ተቀርጸው እየተተገበሩ ነው።
የመማሪያ መጻሕፍት ሥርጭት፣ አዳዲስ ት/ቤቶችን መገንባትና ነባሮችን የማጠናከር እንዲሁም የተማሪዎችን ምገባ ማስፋፋት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የመማር ማስተማር ሒደቱ የጀርባ አጥንት ለሆኑት መምህራን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም በክልሉ የሚገኙ መምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የመስሪያ ቦታና የተገነቡ ቤቶች እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ቢሮው በተለያዩ የወረዳና ገጠር ከተሞች 8 ሺህ 843 መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለምህራን ማስረከቡን ነው የተናገሩት።
የግንባታ ወጪው ከመንግስት፣ ከህብረተሰቡና ከባለሃብቶች የተገኘ መሆኑን አቶ ሃሰን አስረድተዋል።
የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማሳደግ ከመምህራን በተጨማሪ ወላጆችና የትምህርት ማህበረሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በመላኩ ገድፍ