ርዕዮተዓለምን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ጽንፈኝነት የብሔራዊ መግባባት ፈተና ነው – ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማይታረቁ ፍላጎቶችና ቅድሚያ ትኩረት ላይ መግባባት አለመኖር፣ ርዕዮተዓለምን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ጽንፈኝነት እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች መበራከትና የሀብት ውስንነት የብሔራዊ መግባባት ፈተናዎች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ብሔራዊ መግባባት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና በሚል መሪ ሃሳብ ሁለተኛው የፓርላማ የዜጎች ፎረም ተካሂዷል፡፡
በፎረሙ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የብሔራዊ መግባባት ተግዳሮቶች ዙሪያ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሃሳብ÷ ሀገራዊ ምክክርና ብሔራዊ መግባባት በበርካታ ጉዳዮች እንደሚፈተን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የጸጥታና የደህንነት ስጋቶች አሳሳቢ ወደማይሆኑበት ደረጃ ማውረድ ወይም መገደቡ ለሀገራዊ ምክክሩና መግባባቱ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
የማይታረቁ ፍላጎቶችና ቅድሚያ ትኩረት ላይ መግባባት አለመኖር፣ የሚዲያ ሚና እና ሀሰተኛ መረጃ መበራከት፣ ርዕዮተዓለምን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ጽንፈኝነት፣ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች መበራከትና የሀብት ውስንነት፣ የገነገነ መጠራጠርና የቅቡልነት ጉድለትን የሚመለከቱ ጉዳዮች የብሔራዊ መግባባት ፈተናዎች መሆናቸውን በጽሁፋቸው አንስተዋል፡፡
በጉዳዮቹ ላይ የተቀራረበና ለመፍቻውም ቅደም ተከተል ተመሳሳይ አረዳድ መያዝ በሀገራዊ ምክክር እንዲፈጠር የሚፈለገው ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህ ካልሆነ ብሔራዊ መግባባትን ማረጋገጥ አዳጋችና አድካሚ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
ዜጎች የደህንነትና የጸጥታ ስጋት ባለበት አውድ ውስጥ ተረጋግቶ ለመመካከር፣ ጠቃሚ ሃሳብ ለማንሸራሸር ብሎም ከመግባባት ላይ ለመድረስ ይቸገራሉ የሚል ድምዳሜ መኖሩን አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ ከማድረግ አንጻር ጉዳዩ ያለውን ትርጉምና አንድምታ ማየቱ ጠቃሚ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
ፈተናዎችንና ተግዳሮቶችን ተረድቶ መፍትሔ በማስቀመጥ የተሳካ ሀገራዊ ምክክር ማካሄድና ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
የብሔራዊ መግባባት ታሪካዊ መሰረቶች በኢትዮጵያ፣ በአሁኗ ኢትዮጵያ የብሔራዊ መግባባት ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ እና የብሔራዊ መግባባት ሚና በቀጣይ ሀገራዊ ግንባታ ላይ ምን ሚና እንዳለው ምክክር እየተደረገ ነው፡፡