Fana: At a Speed of Life!

ዕለታዊ ሥራዎችን የሚያቀልል ማሽን የሠራው የጅማ ወጣት

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወጣት ጣሂር ዒሳ አገልገሎቱን ጨርሶ ከወዳደቀ ቁሳቁስ የቆሻሻ ማጽጃ እና ሁለገብ የእርሻ ሥራ ማሳለጫ ማሽን ሠርቷል፡፡

የውኃ መፋሳሻ ቦይን ጨምሮ የአካባቢ ጽዳት ሥራ ለመከወን በርካታ የሰው ኃይል መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጸው ወጣቱ÷ የፈጠራ ሥራውን ዕውን ለማድረግ መነሻ ምክንያቱ ይኸው መሆኑን ያነሳል፡፡

በዚሁ መሠረት የተሠራው ማሽን ውኃ መፋሰሻ ቦይ መክፈት፣ ማጽዳት፣ መክደን እንዲሁም ክብደት ያላቸው የተለያዩ ቁሶችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚችል መሆኑን ይናገራል፡፡

ማሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥንነት በርካታ መጠን ያለው ቆሻሻ ማጽዳት ከማስቻሉ ባሻገር÷ እርሻ ማረስ እና ምርት መሰብሰብ (ማጨድ ) እንደሚችል ወጣቱ ይገልጻል፡፡

ነዳጅ ቆጣቢ እንደሆነ የተነገረለት ይህ ማሽን፤ በአንድ ሊትር ናፍጣ ለሦስት ሠዓት የመሥራት አቅም አለው ተብሏል፡፡

ማሽኑን ለመሥራት አገልግሎት አይሰጡም ተብለው የተጣሉ የተለያዩ ቁሳቁሶች እና የውኃ መሳቢያ (ፓምፕ) አገልግሎት ላይ መዋላቸውንም አንስቷል፡፡

ለዚህ ሥራ መሳካት የጅማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና የቅርብ ወዳጆቹ ድጋፍ እንዳልተለየው ገልጿል።

የፈጠራ ሥራውን በተመለከተ ከሚመለከተው አካል ዕውቅና እንዲሰጠው በሂደት ላይ መሆኑንም አመላክቷል፡፡

በቀጣይ የፈጠራ ሥራው ተደራሽ እንዲሆን እና አስፋፍቶ ለመሥራት የመስሪያ ቦታ ችግር እንዳለበት በመጠቆም፤ አካባቢው አሥተዳደር ድጋፍ እንዲያደርግለት ጠይቋል፡፡

በወርቃፈራው ያለው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.