ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት በጥራት እንዲጠናቀቁ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት በጥራት እንዲጠናቀቁ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴርን የ2017 ዓ.ም የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ ሚኒስቴሩ ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት በጥራት እንዲጠናቀቁ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በዘርፉ ጥራትን ለማስጠበቅ ቁጥጥር ማድረግና የህንጻ ደረጃዎችና ኮዶችን የሚመለከቱ መረጃዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።
የአረንጓዴ ልማት ስራዎችም ከሀገራት ጋር ለመወዳደር በሚያስችል መልኩ ደረጃ እንዲኖራቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ፣ በጀትና በጥራት እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎችን በሚመለከት በግማሽ ዓመቱ አጠቃላይ ሽፋን 175 ሺህ 879 ኪሎ ሜትር መሆኑንም አንስተዋል።
የቤቶች ግንባታም በታቀደው መሰረት እየተከናወነ መሆኑን መጠቆማቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።