ሊቨርፑል እና አርሰናል ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተካሄደ የ23ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ሊቨርፑል እና አርሰናል ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ሊቨርፑል ኤፕስዊች ታውንን 4 ለ 1 በማሸነፍ መሪነቱን ባጠናከረበት ጨዋታ የማሸነፊያ ግቦችን ዶሚኒክ ስቦዝላይ፣ መሀመድ ሳላህ እንዲሁም ኮዲ ጋክፖ ሁለት ግቦች ሲያስቆጥሩ ሳላህ በፕሪሚየር ሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች 19 በማድረስ በመሪነት ላይ ተቀምጧል።
በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተደረገ ተጠባቂ ጨዋታ አርሰናል ከ43ኛው ደቂቃ ጀምሮ በ10 ተጫዋቾች ተጫውቶ ዎልቭስን 1 ለ 0 በማሸነፍ በ47 ነጥቦች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ወልቭስ በሁለተኛው አጋማሽ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶበታል።
የዘንድሮው የሊጉ ክስተት የሆነው ኖቲንግሃም ፎረስት በቦርንማውዝ 5 ለ 0 በመሸነፍ ከመሪው ሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ሳይችል ቀርቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ53 ነጥብ ሲመራ አርሰናል በ47 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ኖቲንግሃም ፎረስት ደግሞ በ44 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌሎች የሊጉ ጨዋታዎች ኤቨርተን ብራይተንን 1 ለ 0፣ እንዲሁም ኒውካስል ሳውዝሃምፕተንን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
ምሽት 2፡30 ላይ በቀውስ ውስጥ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ከቸልሲ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።