በትግራይ ክልል የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሲቪክ ማህበራት እና የፀጥታ አመራር አባላትን ያቀፈ አማካሪ ካውንስል ዛሬ ተመስርቷል።
በምስረታው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ እንደገለጹት፥ በክልሉ የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በተለያዩ ዘርፎች የያዛቸው እቅዶች እንዲሳኩ የትግራይ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሲቪክ ማህበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዛሬ የተመሠረተው አማካሪ ካውንስልም የክልሉን ችግሮች በማቃለል በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
በተለይም የዴሞክራሲ ሥርዓትን በማጠናከርና ግልፅነትና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ በአስተዳደሩ የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት ካውንስሉ ትልቅ ድርሻ አለው ነው ያሉት።
በመድረኩ ላይ የካውንስሉ ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢ መመረጣቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።