ውሃ አዘል መሬቶችን በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ጋር ውሃ አዘል መሬቶችን በዘላቂነት ለመጠበቅና ለማስተዳደር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።
ባለስልጣኑ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩትና ከኢትዮጵያ ዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ነው የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረመው፡፡
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ(ኢ/ር) በዚህ ወቅት፥ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ ለዘላቂ ልማትና ብልፅግና ወሳኝ ነው ብለዋል።
በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለያየ ደረጃ ውሃ አዘል መሬት መኖሩን ጠቅሰው፥ ይህም የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ያለውን ሚና ለማሳደግ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የውሃ አዘል መሬቶች ለግብርና እና ቱሪዝም ልማት፣ ለጥናትና ምርምር ስራዎች ጨምሮ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ባለስልጣኑ የውሃ አዘል መሬቶችን በዘላቂነት ለመጠበቅና ለማስተዳደር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የመግባቢያ ስምምነቱም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያ የተቀናጀና ውጤታማ የውሃ አዘል መሬቶች አጠቃቀም መፍጠር ያስችላል ብለዋል።