የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ከ1 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር በላይ ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡ ከ1 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር በላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ የ2017 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀሙን እየገመገመ ነው፡፡
በአፈጻጸም ሪፖርቱ እንደተመላከተው በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 58 ነጥብ 3 በመቶ መሰብሰብ ተችሏል፡፡
ባንኩ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድሥት ወራት 245 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ጠቅላላ የተቀማጭ የገንዘብ መጠኑን ከ1 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር በላይ ማድረስ መቻሉም ተገልጿል፡፡
በዚህም ባንኩ የእቅዱን 147 ነጥብ 6 በመቶ ማሳካቱን ከባንኩ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የተመዘገበው ውጤት ደንበኞች ከባንኩ ጋር ያላቸው ግንኙነትና የባንኩ የአገልግሎት ጥራት መሻሻል ማሳያ መሆኑ ተጠቁሞ ይህም ባንኩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስ የተጣለበትን ትልቅ ኃላፊነት ለመወጣት ያግዘዋል ነው የተባለው፡፡