እስራኤል በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ያላትን ፍላጎት ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ኢ/ር) በውሃ ሀብት ልማትና በኢነርጂ ልማት ዘርፍ በትብብር ለመስራት የፍላጎት መግለጫ ሰነድ ከእስራኤል የኢነርጂ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ኢሊ ኮህን ጋር ተፈራርመዋል፡፡
በፊርማ ስምምነቱ ወቅት ሀብታሙ ኢተፋ (ኢ/ር)÷ የከርሰምድር ውሃ ፍለጋና ማውጣት ፤ የፍሳሽ ማጣራት ቴክኖሎጂዎች እና በታዳሽ ሀይል ልማት ላይ ሊሰሩባቸው የሚችሉ ዘርፎች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የጸሃይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ትግበራ ላይ የእስራኤል ተቋማት ሊሰማሩ የሚችሉባቸው ዘርፎች ናቸው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡ ፡
የእስራኤል የኢነርጂና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ኢሊ ኮህን በበኩላቸው÷በስምምነቱ መሰረት በአቅም ግንባታና በእውቀት ሽግግር፣ በውሃ ልማትና በኢነርጂ ልማት ላይ የእስራኤል ድርጅቶች ተሰማርተው ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡