Fana: At a Speed of Life!

የእግር ኳስ ንጉሱ የ40 ዓመታት ጉዞ..

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፖርቹጋላዊው የአል ናስር አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ረጅም የእግርኳስ ኮከብነቱን አስቀጥሎ በዛሬው እለት 40ኛ አመቱን ደፍኗል፡፡

በእግርኳስ አለም በርካታ ክዋከብቶች የተፈጠሩ ቢሆንም ክብራቸውን አስጠበቀው እና እስከ መጨረሻው የዓለም የእግር ኳስ ቁንጮ ሆነው የዘለቁ ተጨዋቾች ግን ጥቂት ናቸው፡፡

አንዳንድ ተጫወቾች በወጣትነታቸው ባሳዩት ድንቅ የእግርኳስ ክህሎት የዓለምን አይን እና ጆሮ ማግኘት ቢችሉም ብዙም ሳይቆዩ በእድሜ መግፋት፣ በጉዳት እንዲሁም ጤናማ ባልሆን የአኗኗር ዘይቤ ከመድረኩ ሲገለሉ ይስተዋላል፡፡

የ80ዎቹ ኮከብ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በፈረንጆቹ 1997 ጫማ ሲሰቅል 37 ዓመቱ የነበረ ሲሆን የሱ ተቀናቃኝ የነበረው ብራዚላዊው ፔሌ በ36 ዓመቱ አግር ኳስ በቃኝ ብሏል፡፡

ከእግር ኳስ አቢዮተኛዋ ሀገር ብራዚል ምድር የፈለቀው ሮናልዲኒሆ ጎቾ ዲያሲስ ሞሬራም ቢሆን ታይቶ የጠፋ እስኪመስል ድረስ የጥቂት ዓመታት የእግርኳስ ክስተት ሆኖ በ37 ዓመቱ እግርኳስ አቁሟል፡፡

ሌላኛው ብረዚላዊ ኔይማር ጁኒየርም ቢሆን በትላንትናው እለት 33ተኛ አመቱን የደፈነ ሲሆን እግር ኳስን ወደ ጀመረበት የብራዚሉ ሳንቶስ ክለብ በመመለስ ጫማ ለመስቀል እያሟሟቀ ይመስላል፡፡

በአንጻሩ በርካቶች የብቃት ጣሪያቸው  ወርዶ እግ ኳስን ለማቆም በሚያስቡበት አሊያም በትንሽ ሊግ እና ክለብ ለመጫወት በሚያስቡበት የእድሜ እርከን ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶሳንቶስ አቪዬሮ ከ30-39 ባለው እዴሜው ለሪያል ማድሪድ፣ማቼስተር ዩናይትድ እና አልናስር ባደረጋቸው 543 ጨዋታዎች 460 ግቦችን ሲያስቆጥር 102 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማቀበል ችሏል፡፡

አይበገሬው የኳስ ቀበኛ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳስ 40 ዓመታትን ዘልቆ ዛሬም በኮከብነቱ እና ተፅእኖ ፈጣሪነቱ ቀጥሏል፡፡

40ኛ ዓመቱን አስመልከቶ ከስፔኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላ ሲክስታ ጋር ቆይታ ያደረገው ሮናልዶ፣በእድሜ ምክንያት ምንም አይነት የአካል ለውጥ ሆነ ድካም አይታይብኝም ብሏል፡፡

“እግር ኳስ የኔን አይነት ኮከብ መልሳ ማግኘት አትችልም “ሲል የተናገረው ሮናልዶ” በተፈጥሮ ግራ እግር ሳልሆን በግራ እግር በማስቆጠር ታሪክ ያለኝ ተጫዋች ነኝ፣ በዚህም በእግር ኳስ የተዋጣለት አጥቂ እኔ ነኝ” ሲል ራሱን አሞካሽቷል፡፡

ሮናልዶ በ40 ዓመታት ውስጥ 217 ጊዜ ለፖርቹጋል በመሰለፍ 135 ጎሎችን በማስቆጠር የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን የምንጊዜም ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነው፡፡

በክለብ ደረጃ ሮናልዶ በስፖርቲንግ ሊዝበን፣ማንቼስተር ዩናይትድ፣ሪያል ማድሪድ፣ጁቬንቲዩስ እና አል ናስር በአጠቃላይ 923 ጎሎችን በማስቆጠር በእግር ኳስ ታሪክ የምንጊዜም ባለ ብዙ ጎል ተጫዋችም ነው፡፡

ከዚህ ውስጥም 171 ጎሎችን በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም 151 ጎሎችን ደግሞ በጭንቅላቱ ገጭቶ በማስቆጠር የክበረ ወሰን ባለቤት ነው፡፡

በዛሬው እለት 40ኛ ዓመቱን የደፈነው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአለም ከ900 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በግል እንደሚደግፉት የተገለጸ ሲሆን ሮናልዶ አሁን ላይ የአውሮፓ እና የአለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ጨምሮ በብዙ አለማቀፍ መድረኮች እንደሚሰልፍ ይጠበቃል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.