ጨፌ ኦሮሚያ 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ የ4ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን በአዳማ ከተማ ገልመ አባገዳ ማካሄድ ጀምሯል።
በአባገዳዎች ምርቃት የጀመረው መደበኛ ጉባኤው በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባኤው የክልሉን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ÷ከሰላም አንፃር በተከወኑ ተግባራት መልካም ውጤቶች ያስገኘ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም በቅርቡ በክልሉ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተረጋጋ ሰላም መስፈኑን አንስተዋል።
የመንግስትና የህዝብን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማህበረሰቡ ለተመለሱ አካላትም ክልሉ ትልቅ ክብርና ምስጋና የሚያቀርብ ስለመሆኑም ገልፀዋል።
አሁንም ወደ ሰላማዊ መንገድ ያልተመለሱ የታጠቁ አካላት የአባገዳዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እንዲመለሱ ያሳሰቡ ሲሆን መንግስት አሁንም የዘረጋው የሰላም እጅ እንዳልታጠፈም አረጋግጠዋል።
በታምራት ደለሊ