Fana: At a Speed of Life!

ፊፋ የኮንጎ ሪፐብሊክንና የፓኪስታንን እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች አገደ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የኮንጎ ሪፐብሊክን እና የፓኪስታንን እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማገዱ ተሰማ።

የኮንጎ እግር ኳስ ማህበር (ፌኮፉት) ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ ውድድሮች የታገደው በተቋሙ ውስጥ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብቷል በሚል መሆኑን ፊፋ አስታውቋል።

ፊፋ ሶስተኛ ወገን ያለው የአገሪቱን መንግስት ሲሆን ጣልቃ ገብነቱ ፊፋ እና የሀገሪቱ እግር ኳስ ማህበር ለመተዳደሪያነት ውል የገቡትን ህግ የጣሰ ነው ሲል ጠቅሷል።

የኮንጎ ብራዛቪል መንግስት የሀገሪቱን እግር ኳስ ማህበር ተግባራት የሚከታተል ልዩ ኮሚቴ ማቋቋሙ የገለጸው ፊፋ ድርጊቱ የተቋሙን ህግ እና አሰራር የሚጥስ ነው ብሏል።

በሌላ በኩል ፊፋ የፓኪስታን እግር ኳስ ፌደሬሽን የአስተዳደር ማሻሻያ ተግባራዊ ባለማድረጉ እና የሀገሪቱ መንግስት በፌደሬሽኑ ውስጥ በተደጋጋሚ ጣልቃ እየገባ ነው በሚል ምክንያት በማንኛውም ዓለም አቀፍ ውድድር እንዳይሳተፍ የዕግድ ውሳኔ ማስተላለፉ ወርልድ ሶከር ቶክ ዘግቧል።

በሀገሪቱ አግር ኳስ ፌደሬሽን እ.ኤ.አ በ2017 እና በ2021 በተመሳሳይ ህግ ጥሰት አግድ ተጥሎበት አንደነበር ተጠቅሷል።

ይህን ውሳኔ ተከትሎ ፊፋ በዓለም እግር ኳስ ውድድሮች እንዳይሳተፉ ያገዳቸው ሀገራት ቁጥር ሶስት ደርሷል።

ከዚህ በፊት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስት መግባቷን ተከትሎ ከእግር ኳስ ውድደሮች መታገዷ ይታወሳል።

የሶስቱ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች እና የሀገር ውስጥ እግር ኳስ ቡድኖች ማንኛውም ዓይነት ዓለም አቀፍ ውድድር ማድረግ አይችሉም።

እገዳው እንዲነሳ ለሁለቱም ሀገራት እግር ኳስ አስተዳዳሪ ተቋማት እና መንግስታት ቀድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.