Fana: At a Speed of Life!

በሴቶችና ሕፃናት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ አስከፊ የሆነውንና በሴቶችና ሕፃናት ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጉዳት ለመቀነስ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ገለጹ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና ከጨፌ ኦሮሚያ ሴት አባላት ጋር በሴቶችና ሕፃናት ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጉዳት መቀነስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ÷በሴቶችና ሕፃናት ላይ እየደረሰ የሚገኘው ጉዳትና ሞት ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየሰፋ መምጣቱን አንስተዋል።

በመሆኑም ችግሩ እንዲቀረፍ ተጠያቂነትን ለማስፈን የወጡ ሕጎች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑና ተመጣጣኝ ፍርድ መሰጠት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረሀማን በበኩላቸው÷ችግሩ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ መሆኑን በማንሳትም በተለይም በምስራቅ ሀረርጌና ምስራቅ ባሌ ችግሩ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ስለሆነም የምክርቤት አባላቱ ጉዳቱን መቀነስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መስራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

የሴቶች ጥቃትና ጉዳት በሀገር ግንባታ እንዲሁም በማህበራዊ፣ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሂደቶች ላይ ጫና የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።

እየደረሰ የሚገኘው ጉዳት እንዲቀንስ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ መብራት ባጫ ናቸው፡፡

ደንቦችን ተግባራዊ በማድረግና የፍርድ አሰጣጡን በማሻሻል እየደረሰ የሚገኘው ጉዳት እንዲቀረፍ መሰራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በታምራት ደለሊ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.