Fana: At a Speed of Life!

ለስርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን ለማብቃት ዩኤን ውመን ድጋፌን አጠናክራለሁ አለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ከዩኤን ውመን የምስራቅ አፍሪካ እና የደቡባዊ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ማዳም አና ሙታቫቲ ጋር ተወያይተዋል።

ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎቹ ውይይት ያደረጉት ከስርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን ከማብቃት ጋር በተያያዘ በተጀመሩና ቀጣይ በጋራ ሊሰሩ በሚችሉ አዳዲስ ኢኒሼቲቮች ዙሪያ ነው ተብሏል።

ኤርጎጌ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ሚኒስቴሩ የሴቶችን አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለማሳደግ እንዲሁም ሴቶችን ለማብቃት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

ከዩኤን ውመን ጋር በመተባበርም ብሔራዊ የሴቶች ፖሊሲ ክለሳ መደረጉን፣ የቤጂንግ+30 መግለጫና የድርጊት መርሐ-ግብር ሀገራዊ ሪፖርት ዝግጅት ተጠናቅቆ በወቅቱ መላክ መቻሉን፣ የሴቶች የልማት ህብረትን የማደራጀትና የማጠናከር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በግጭት የተጎዱ ሴቶችን በሰላምና ደህንነት ረገድ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጉላት፣ ግጭትን ለመከላከል እና መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ ብሔራዊ የድርጊት መርሐ-ግብር ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ለዚህም በዩኤን ውመን በኩል እየተደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ሚኒስቴሩ ሴቶችን በግብርና በዲጂታል ቴክኖሎጂ መስክ እንዲሰማሩና ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅ ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ መያዙን ገልፀው ፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስተሯ ጠይቀዋል።

የዩኤን ውመን የምስራቅ አፍሪካ እና የደቡባዊ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ማዳም አና ሙታቫቲ በበኩላቸው፥ ሚኒስቴሩ ለሴቶች መብት መከበር፣ ለስርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን ለማብቃት የተጓዘውን ርቀትና የተገኘውን ውጤት አድንቀዋል።

በቀጣይም ዩኤን ውመን ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን ወደ ስራ በማስገባት ለሴቶች የተሻለ ተጠቃሚነት በጋራ እንደሚሰራና ድጋፍም እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.