አመራሩ በፓርቲው ጉባዔ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚ ማድረግ አለበት – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የተላለፉ ውሳኔዎች እንዲተገበሩ ሁሉም አመራር የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተወያዩ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ፥በጉባኤዉ አጠቃላይ አሁናዊ፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ ትንተና ቀርቦ በጥልቀት ምክክር መደረጉን ጠቅሰው አመራሩ ውስጥ ያለው የውስጥ ጥንካሬ ሊሻሻል እንደሚገባ ተመላክቷል ብለዋል።
የጋራ ራዕይ በመያዝ ወደ ተግባር የሚገባ ቁርጠኛ አመራር አስፈላጊ መሆኑ በጉባኤው አፅንኦት የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነም አንስተዋል።
“ከቃል እስከ ባህል” እሳቤን መነሻ በማድረግ ስራዎችን ባህል በማድረግ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ በማለፍ ፓርቲው በጉባኤው ያሳለፋቸውን ዉሳኔዎች ተፈፃሚ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃልም ብለዋል።
አመራሩ በ2018 ዓ.ም ከተስፋ ወደ የሚጨበጥ ብርሃን እንዲሁም በ2023 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን የተቀመጠውን ዕቅድ የማሳካት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ተገንዝቦ እንዲንቀሳቀስ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ፥ በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የተወሰኑ ውኔዎች እና የተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ የመወያያ ሰነድ አቅርበው ውይይት መደረጉንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡