ሃማስ እስራኤላዊያን ታጋቾችን ሙሉ ለሙሉ ካለቀቀ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ይቋረጣል – ፕሬዚዳንት ትራምፕ
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃመስ እስራኤላዊያን ታጋቾችን ሙሉ ለሙሉ የማይለቅ ከሆነ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በማቋረጥ ዳግም ጦርነት እንደሚከፈት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ፡፡
የበርካታ ንጹሃንን ሕይወት የቀጠፈውና ሚሊየኖችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ከወር በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ጊዜያዊ እፎይታን መፍጠሩ ይታወሳል፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተጀመረበት ከፈረንጆቹ ጥር 19 ጀምሮ እስካሁን 16 እስራኤላዊያን እና 3 የታይላንድ ዜጎች የተለቀቁ ሲሆን÷በምትኩ 566 ፍልስጤማውያን እስረኞች ነጻ ወጥተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሃማስ እስራኤል በስምምነቱ የተካተቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ጥሳለች በሚል ቀሪ ታጋቾችን የመልቀቁ ሒደት እንደሚያዘገይ አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃማስ እስከ መጪው ቅዳሜ እስራኤላዊያን ታጋቾችን ሙሉ ለሙሉ የማይለቅ ከሆነ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንደሚያበቃና በጋዛ ዳግም ጦርነት እንደሚታወጅ አስጠንቅቀዋል፡፡
የሃማስ ቃል አቀባይ ሳሚ አቡ ዙህሪ በበኩላቸው÷ማስፈራራት ሁኔታዎችን ይበልጥ ከማወሳሰብ የዘለለ ዋጋ የለውም ሲሉ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ ዛቻ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ÷ሃማስ በጋዛ የሚገኙ ታጋቾችን እንዲለቅ የተቻለው ሁሉ ተደርጎ መጪውን አስከፊ ጦርነት ማስቀረት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
እስራኤል በበኩሏሃማስ ስምምነቱን ጥሷል በማለት የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በጋዛ ለሚኖረው የትኛውም ሁኔታ በተጠንቀቅ እና በከፍተኛ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ አስታውቃለች፡፡
በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዮርዳኖስ ንጉስ አብዱላህ ጋር ሊወያዩ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዮርዳኖስ እና ግብጽ የዶናልድ ትራምፕን ጋዛን መልሶ መገንባት እና ፍልስጤማዊያንን በሁለቱ ሀገራት እንዲሰፍሩ የማድረግ ሃሳብ የማይቀበሉ ከሆነ ለሀገራቱ የሚደረገውን እርዳታ እንደሚያቋርጡማሳሰባችውን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡
በአቤል ንዋይ