ከ66 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የኤሌክትሪክ ኬብል ግዢ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ66 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የኤሌክትሪክ ኬብል ግዢ ለመፈፀም የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የኬብል ግዢ ስምምነቱ የተፈረመው ቲቢኤ ዲያንግ ኬብል ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር ሲሆን÷በስምምነቱ መሠረት የኬብል አቅርቦቱ በዘጠኝ ወራት ተጠናቆ የሚቀርብ ይሆናል ተብሏል፡፡
የኬብል ግዢው የተፈፀመው በዋናነት በገጠር እና በከተማ ያለውን የአዲስ ኃይል ጥያቄ ለማስተናገድ እንዲሁም የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ለማከናወን መሆኑም ተገልጿል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ(ኢ/ር) ÷ስምምነቱ በተለይ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ አዲስ ኃይል ጠያቂ ደንበኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በቲቢኤ ዲያንግ ኬብል ኩባንያ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት ጅልበርት ዛዎ በበኩላቸው÷ከአገልግሎቱ ጋር ለመስራት ዕድሉን በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ቃላቸውን ጠብቀው እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡
ለኬብል ግዢ ስምምነቱ 66 ሚሊየን 123 ሺህ 842 የአሜሪካን ዶላር እና 37 ሚሊየን 233 ሺህ 62 ብር ወጪ የሚደረግ ሲሆን÷ወጪው ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚሸፈን ይሆናልም ተብሏል፡፡