ምርታማነትን ማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራሮች በ2ኛው የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባዔ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ላይ ተወያይተዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በፓርቲው አቅጣጫ የተቀመጡ ጉዳዮች ከተገኙ ድሎች እና ካጋጠሙ ችግሮች መነሻ ሃሳብ የተወሰዱ ናቸው።
እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የተመዘገቡ ውጤቶች የሚያኩራሩ ሳይሆን ወደፊት በሚቀሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መስራት እንደሚገባ የሚያመላክቱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በክልሉ የስራ ባህልን በማሻሻል ከተረጂነት ለመውጣት የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር ተገቢ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከጎታች እሳቤዎች በመውጣት ሕዝቡን ማሻገር በሚያስችሉ ተግባራት ላይ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል ።
በቀጣይ ምርታማነትን ማሳደግ እና ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ የዲፕሎማሲ ጥረት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።