Fana: At a Speed of Life!

በተወሰዱ የለውጥ ርምጃዎች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስኮች ድሎች ተመዝግበዋል – አቶ አደም ፋራህ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 6 ዓመታት በብልፅግና ፓርቲ በሚመራው መንግስት በተወሰዱ የለውጥ ርምጃዎች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስኮች ተጨባጭ ድሎች ማስመዝገብ ተችሏል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዐት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።

በአቶ አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዓለም መንግስታት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡

3ኛ ቀኑን የያዘውና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም መንግስታት ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያላትን መንግስታዊ የአስተዳደር ልምዶች አቅርባለች።

ልምዶቹን ያቀረቡት አቶ አደም÷ ባለፉት 6 ዓመታት በብልፅግና ፓርቲ በሚመራው መንግስት በተወሰዱ የለውጥ ርምጃዎች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች ተጨባጭ ድሎችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።

በተለይም በድህነት ቅነሳ፣ በሰው ተኮር ተግባራት፣ አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ እመርታዎችን በመፍጠር፣ በምግብ ራስን ለመቻል በተደረጉ ጥረቶች እንዲሁም ያልታዩ ሀገራዊ ፀጋዎችን ለይቶ በመጠቀም ረገድ የተገኙ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ስልታዊ አይበገሬነትን ለማረጋገጥም ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ ተግባራዊ በተደረጉ ርምጃዎች አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ ለውስብስብ ችግሮች ቀላል መፍትሄዎችን ማፍለቅ መቻሉን መናገራቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህ ሀገራዊ ውጥን ግቡን እንዲመታ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን የመሰሉ ሀገራት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮችን በማሰልጠን ድጋፍ እያደረጉ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከፍተኛ አክብሮት እንዳላት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በተግዳሮት የማይናወጥ ቋሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ማህበራዊ ዋስትና እና ጠንካራ መንግስታዊ አስተዳደርን መገንባት ስልታዊ አይበገሬነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በማመን ሀገር በቀል በሆነው የመደመር እሳቤ ተመርታ ወደ ብልፅግና የምታደርገው ጉዞ ውጤታማ መሆኑንም አስረድተዋል።

በቀጣይም የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ኢትዮጵያ መርህን ባከበረ መልኩ ከሀገራት ጋር ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ለመስራት በሯ ክፍት እንደሆነ አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.