ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩሲያና ቻይና አቻዎቻቸው ጋር በወታደራዊ በጀት ቅነሳ ዙሪያ መወያየት እንደሚፈልጉ ተናገሩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ሺንፒንግ ጋር የሦስቱንም ሀገራት የኒውክሌር ክምችት ለመቀነስ እና የወታደራዊ በጀታቸውን በግማሽ በመቀነስ ላይ ለመወያየት ሀሳብ አቅርበዋል።
ትራምፕ በሰጡት መግለጫ ከሀገራቱ መሪዎች ጋር ነገሮች ሲረጋጉ እንደሚገናኙ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡
ዓለምን ሊያጠፋ የሚችል የዋሽንግተን ጦር እያለን አዲስ የኒውክሌር ጦር ለመገንባት ምንም ምክንያት የለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ የህዝብ ገንዘብ የበለጠ ውጤታማ በሆኑ ሌሎች ነገሮች ላይ ማዋል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ከቀናት በፊት ከፑቲን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት የጦር መሳሪያ ቅነሳ ላይ መምከራቸውም ታውቋል፡፡
አሜሪካ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዋን ከተጠቀመች ለዓለም መጥፋት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።
አሜሪካ እና ሩሲያ ከዓለም በኒውክሌር ክምችት በቀዳሚነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ለትርፍ ያልተቋቋመው የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ማህበርን ጠቅሶ የዘገበው አልጀዚራ፤ ቻይና ደግሞ ሁለቱን ሀገራት ትከተላለች ብሏል፡፡
የአሜሪካ ኮንግረስ ለ2025 በጀት ዓመት 895 ቢሊየን ዶላር ለወታደራዊ በጀት ሲመድብ፥ ቻይና 185 ቢሊየን ዶላር ትበጅታለች ተብሎ ይጠበቃል።
የዓለም አቀፍ የስትራቴጂ ጥናት ተቋም ባወጣው ግምት መሠረት ባለፈው ዓመት የሩሲያ ወታደራዊ ወጪ 145 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር መድረሱን አውስቷል።
አሜሪካ በዓለም ካሉ ሀገራት ከፍተኛ ወታደራዊ በጀት የምትመድብ ሀገር ናት።
በመሰረት አወቀ