ኢትዮጵያ ኢጋድ ግጭቶችን ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት ድጋፍ ታደርጋለች – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በቀጣናው የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት ከኢትዮጵያ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ ለኢጋድ ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ እና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለአካባቢው ልማትና ኢኮኖሚ ትስስር ኢትዮጵያ ያላትን ቁልፍ ሚና አንስተዋል።
የኢጋድ ስትራቴጂክ ግቦች ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን አንስተው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ከኢጋድ ጋር የበለጠ በቅርበት እንደምትሰራ ጠቁመዋል።
የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አዲሱን የኢጋድ ስምምነት በማጽደቋ አመስግነው ሀገሪቱ እንደ አባል ሀገር የምታደርገውን ወሳኝ ድጋፍና ትብብር አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።