Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝብ ሰላምና መረጋጋት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝብ ሰላምና መረጋጋት በሁሉም መስክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናገሩ፡፡

በሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ የሚመክር የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአፍሪካ ህብረትና ኢጋድ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ጉባኤው የሱዳንን ቀውስ ለማስቆም በተለይም በረመዳን የጾም ወቅት የተኩስ አቁም እንዲደረስ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ለሱዳናውያን እንዲደርስ ለማስቻል የተደረገ ነው።

በጉባኤው የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና ሱዳን ጎረቤት ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ ጠንካራ ቁርኝት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሱዳን ህዝብ ጎን ትቆማለች፤ ባላት አቅምም የምታደረገውን የሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ 15 ሚሊየን ዶላር ለግሳለች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)።

ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለሱዳን ዘላቂ ሰላም መስፈን እንዲሁም የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ለሰላማዊ መፍትሄ እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በበኩሏ ተጨማሪ 200 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ሰጥታለች።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ እያደረጉ ላሉት ጥረት አመስግነዋል።

በጉባኤው የኬንያው ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቡት ቢን ናህያን አልናህያን፣ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተካፍለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሱዳን አጠቃላይ ህዝብ 64 በመቶ የሚሆነው ድጋፍ እንደሚፈልጉ ተጠቅሷል።

በምስክር ስናፍቅ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.