Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሕጻናት መብት መከበርና ደህንነት መረጋገጥ የሰራችው ስራ ለአፍሪካ ሀገራት ልምድ እንደሚሆን ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሕጻናት ሁለንተናዊ መብት መከበርና ማህበራዊ ደህንነት መረጋገጥ የሰራችው ስራ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድ እንደሚሆን ተገለፀ።

ከአፍሪካ ሕፃናት መብት ደህንነት ኮሚቴ ሊቀመንበርና የልዑካን ቡድናቸውን ጋር የተወያዩት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ የአፍሪካ የህፃናት መብትና ደህንነት ቻርተርን ተቀብለው ካፀደቁ 51 ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ለህጻናት ሁለንተናዊ መብት መከበር ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለስምምነቶቹ አፈጻጸምና ስኬታማነት እገዛ የሚያደርጉ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ሀገራዊና አህጉራዊ ሃላፊነቷን ለመወጣት ያለሳለሰ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል እና ለማስቀረትም ስትሰራ ቆይታለች ማለታቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የአፍሪካ ሕፃናት መብት ደህንነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ዊልሰን አዳዎ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በሕጻናት ሁለንተናዊ መብት መከበርና ማህበራዊ ደህንነት መረጋገጥ የሰራችው ስራ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሕፃናት መብት መከበር፣ የሕፃናት ተሳትፎና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ አህጉራዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀጥል እገዛ እንድታደርግም ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.