Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርዓት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርዓት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርዓት ሰብሳቢ አብዱልመጅድ ተቡን ገለጹ።

የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርዓት 3ኛ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ እና 34ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ሲካሄድ፤ የተገመገሙ ሀገራትን ሪፖርት አድምጦ አጽድቋል።

እንዲሁም በበጎ ፈቃደኝነት ለመገምገም ያመለከቱ ሀገራትን ጥያቄ የተቀበለ ሲሆን፥ በተጨማሪም የአቻ መገማገሚያ ስርዓት መድረኩን የአንድ አመት የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት አጽድቋል።

የአቻ ግምገማ ስርዓት ሰብሳቢው ፕሬዚዳንት አብዱልመጅድ ተቡን በዚሁ ወቅት፥ ስርዓቱ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት አስፈላጊ መሳሪያ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርዓት መልካም አስተዳደርን ለማጠናከር ጠቃሚ ዘዴ እንደሆነ በማስታወቅ፥ አባል ሀገራት በፈቃደኝነት ለዚህ ስርዓት መዋጮ በመክፈል ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት በበኩላቸው፥ የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርዓት ስኬት የሚጀምረው ከ20 ዓመታት በፊት ከተደረሰው ስምምነት አንስቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአቻ ግምገማው ለመሳተፍ የሀገራት ፍላጎት እየተጠናከረ መምጣቱንና ተቋማዊ መሆኑን በመጥቀስ፥ ስርዓቱ በፈቃደኝነት ለሚገመገሙ ሀገራት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።

የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርዓት በአህጉሪቱ የመንግስት አስተዳደርን ለማሻሻል ወሳኝ መሣሪያ ነው ያሉት ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው።

በአህጉሪቱ ሰላም፣ ብልጽግና እና ውህደትን ለመፍጠር ወሳኝ ዘዴ መሆኑን ገልጸው፥ የአጀንዳ 2063 ራዕይን ለማስፈጸም ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.