የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት የዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት አራት የዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችለውን የድጋፍ ስምምነት ተፈራርሟል።
ስምምነቱ የተከናወነው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የካሊፍ ቢን ዛይድ አል-ናሃያን ፋውንዴሽን ጋር መሆኑ ተገልጿል።
ስምምነቱን ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና እና የፋውንዴሽኑ ዳይሬክተር ጀነራል ሙሃመድ ሃጂ አልከሆሪ የተፈራረሙ ሲሆን÷ በስምምነቱ ላይ ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የመጡ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የድጋፍ ስምምነቱ በተለያዩ የክልል ከተሞች ደረጃውን የጠበቀና ሙሉ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው አራት የዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ መረጃ አመላክቷል።
ቃሊቲ አካባቢ ተገንብቶ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የሚገኘውን የዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ጽሕፈት ቤቱ በመሰል ድጋፍ ገንብቶ ማስረከቡ የሚታወስ ነው።