Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ – ከቅኝ ግዛት ወደ ኢኮኖሚያዊ ነጻነት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ በተለያዩ ጊዜያት ለሀገራቸው ብሎም ለአህጉራቸው ዋጋ የከፈሉ ድንቅ መሪዎችን አፍርታለች፡፡

አፍሪካ በድህነት፣ በጦርነት፣ በመልካም አስተዳደር ጉድለት እና በሙስና ስሟን ከሰፈረበት መዝገብ ለመፋቅ በተለያዩ ጊዜ በእልህ የተነሱላት ልጆች ነበሯት፤ አሏትም፡፡

አፍሪካ ከቅኝ ግዛት እንድትላቀቅና ኢኮኖሚዋ እንዲያንሰራራ ለህይወታቸው ሳይሳሱ በትጋት አገልግለዋታል።

ቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሴ

ፓን አፍሪካዊ የነበሩት ቀኃሥ አፍሪካን ከአፍሪካውያን እና ከተቀረው የዓለም ማህበረሰብ ጋር በሰፊው በማስተሳሰር ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ብቃታቸውን ለዓለም ማስመስከር የቻሉ ናቸው።

በዚህም ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር አባል እንድትሆን አድርገዋል። በፈረንጆቹ 1963 ደግሞ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች እና የድርጅቱ የመጀመሪያ ሊቀ-መንበርም ነበሩ፡፡

ለአፍሪካውያን አንድነትም መሰረት ከጣሉ ቀደምት አባቶች መካከልም በግንባር ቀደምትነት ሥማቸው ይነሳል።

ኩዋሜ ንክሩማህ

ክዋሜ ንክሩማህ የጋና የመጀመሪያው የሀገሪቱ ተወላጅ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ፥ ሀገራቸውን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንድትወጣ በማድረግ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረትም ከመስራቾቹ አንዱ ነበሩ፡፡

ንክሩማህ ለ12 ዓመታት በውጭ ሀገር ተምረው ወደ ሀገራቸው ጋና በመመለስ ከቅኝ ግዛት ነጻ እንድትሆን ታግለዋል።

በዚህም ግዙፍ ፕሮጀክቶችንና የልማት ስራዎችን በፕሬዚዳንትነት ቆይታቸው ሰርተዋል።

ጁሊየስ ኔሬሬ

ጁሊየስ ኔሬሬ የታንዛኒያ (የቀድሞዋ ታንጋኒካ) ከፈረንጆቹ 1961 እስከ 1985 የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። ፓን-አፍሪካዊው ኔሬሬ በ1953 ታንጋኒካ የአፍሪካ ብሔራዊ ህብረት ለመመስረት ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶም ታንጋኒካ 1961 ነፃነቷን አግኝታለች።

በተጨማሪም ኔሬሬ በ1964 ዛንዚባር እና ታንጋኒካን አንድ በማድረግ ታንዛኒያን በማዋለድ ሂደት ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

ፓትሪስ ሉሙምባ

ፓትሪስ ሉሙምባ አብዮታዊ የኮንጎ ፖለቲከኛ ሲሆኑ፥ የሀገሪቱ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትርም ናቸው፡፡ ሉሙምባ እንግሊዛዊ ዜግነት በነበራቸው ወቅትም የኮንጎ ንግድ ህብረት ፕሬዚዳንት በመሆን ማገልገላቸው ይወሳል።

ወደ ኮንጎ ከተመለሱ በኋላም የኮንጎ ብሔራዊ ንቅናቄን (ኤም ኤን ሲ) በመመስረት የፓን አፍሪካን ርዕዮተ-ዓለምን በመጠቀም ለሀገራቸው ነፃነት ታግለዋል።

አሁን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመባል የምትታወቀው ኮንጎ በ1961 ነጻ ሀገር ሆና እንድትቀጥል ምክንያትም ነበሩ፡፡ ሉሙምባ በድንቅ ስብዕና እና በመግባባት ችሎታቸው ከሚነሱ ምስጉን መሪወች መካከል በግንባር ቀደምነት ይነሳሉ፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ገና በ35 ዓመታቸው በምዕራባውያን እና በውስጥ ኃይሎች በተቀነባበረ ሴራ መገደላቸው እስካሁን የሀገሬው ሰው የእግር እሳት ነው፡፡

ጆሞ ኬኒያታ

የፀረ-ቅኝ ግዛት ታጋይ እና አታጋይ የነበሩት ጆሞ ኬኒያታ የመጀመሪያው የኬንያ ፕሬዚዳንት እና ከ1963 እስከ 1964 ደግሞ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። በዚያን ወቅት እንግሊዝ ባህር አቋርጣ ድንበር ጥሳ ልግዛችሁ ስትል አሻፈረኝ በሚለው ትግላቸው ይታወሳሉ፡፡

ዘረኝነትንና መድሎን አምርረው የሚጠሉት ኬኒያታ ሀገራቸው ከቅኝ ግዛት ለመውጣቷ ትልቅ ሚና የተወጡ ፓን አፍሪካኒስት ነበሩ።

በተጨማሪም በሀገራቸው ህዝቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍን እና ኬኒያ የአፍሪካ ህብረት አባል እንድትሆን አድርገዋል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ

ኔልሰን ማንዴላ የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፥ ከዚያ በፊት አፓርታይድን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ለ27 ዓመት የወጣትነት ጊዜያቸውን በእስር አሳልፈዋል፡፡

ከረጅም ዓመታት እስር በኋላ የፓርቲያቸው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ (ኤ ኤን ሲ) ፓርቲ በፈረንጆቹ 1994 የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎም ሀገራቸውን መምራት የሚችሉበትን እድል አግኝተዋል።

ምርጫውም በደቡብ አፍሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ እንደሆነ ይነገርለታል።

ማንዴላ የደቡብ አፍሪካውያን ሁሉ የቤተሰብ አባል ናቸው፤ የፍቅርና የይቅርታ ምሳሌ፣ ወጣትነታቸውን ለሀገራቸው መስዋዕት ያደረጉ የነጻነት ቀንዲል የአፍሪካ ብርቅ ልጅ ናቸው፡፡

በአፓርታይድ ዘመን የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚያጣራ የእርቅ ኮሚሽን በማቋቋም ለ27 ዓመታት በብረት አጥር ውስጥ በስቃይ ላኖሯቸው፤ እድሜያቸውን ቀምተው ግፍ ለፈጸሙባቸው በቀል ሳይሆን ምህረት አድርገው ለዓለም ይቅርታን እና የይቅርታን አስፈላጊነት ”ይቅር ብያችኋለሁ” በማለት አሳይተዋል።

ማንዴላ ለዓስርት ዓመታት የዘለቀውን የአፓርታይድ ጭካኔን በመታገልና በደቡብ አፍሪካ ሰላም አምጥተዋል።

ይህም አህጉሪቱ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳለችበት የረሃብ፣ የችግር፣ የድህነትን ምስል የሚያፈራርስና እውነተኛዋን አፍሪካ ለማሳየት የሚያስችል ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት አፍሪካ የሚደርስባትን ኢ-ፍትሃዊነትና ቀጥታ ያልሆነ ቅኝ ግዛትን የሚያጋልጥና የሚያስገነዝብ ይሆናል፡፡

ለአፍሪካ አንድነት መሰረት በመጣል ቀደምት አባቶች ብዙ ለፍተዋል። በአሁን ዘመን ያሉ መሪዎች ደግሞ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታትን ዒላማ አድርገው አህጉራዊውን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ፈተናዎች ለማለፍ እየሰሩ ይገኛል።

በተለይም ደግሞ የአፍሪካ ድምጽ በዓለም መድረክ ይሰማ ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የአህጉሩ መሪዎች ዘርፈ ብዙ ትግል እያደረጉ ይገኛል።

ጥረታቸውም ፍሬ እያፈራ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል።

ፓን-አፍሪካኒዝም የሁሉም አፍሪካዊ የአህጉራዊ አንድነት ማጥበቂያ ገመድም ሊሆን ይገባል።

ይህንና መሰል የአፍሪካ አጀንዳዎችን ለመተግበር ያለመ 46ኛው የአፍሪካ ኀብረት መደበኛ የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን፤ 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.