ባንኩ ለአፍሪካ የሥርዓተ ምግብ መስተካከል የሚያደገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአህጉሪቱ የሥርዓተ ምግብ መስተካከል የሚያደገውን ድጋፍ አጠናክሮ አንደሚቀጥል ገለጸ።
የአፍሪካን የሥርዓተ ምግብ ለማስተካከል ያለመ መድረክ “ከፖሊሲ ወደ ተግባር” በሚል መሪ ሀሳብ ከ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ኔና ኑዋቡፋ ተቋማቸው ለአፍሪካ የሥርዓተ ምግብ መስተካከል የሚያደገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
እስካሁን በተከናወኑ ተግባራትም ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ዳይሬክተር ጄነራል ኩ ዶንግዩን በበኩላቸው የአፍሪካ ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል ድርጅቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ የባለድርሻዎች የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ከረሀብ ነፃ ዓለም የመፍጠር ግብ አሁንም በሚፈለገው ደረጃ እየሄደ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ ተጨባጭ የድርጊት መርሀ-ግብር እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አሁንም በአፍሪካ አሳሳቢ ፈተና ሆኖ አህጉሪቱ በዓመት 153 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ለምርታማነት እና ለኢኮኖሚ እድገት ኪሳራ እየተዳረገች መሆኑ ተጠቁሟል።
አፍሪካ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት በማፋጠን ላይ ያተኩራል የተባለው መድረኩ በጉዳዩ ዙሪያ የጋራ አቋም ለመያዝ ያለመ መሆኑም ተመላክቷል።
መድረኩን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን፣ አፍሪካ ልማት ባንክ፣ ሌሴቶ እና ኮትዲቯር በጋራ ማዘጋጀታቸው ተገልጿል።
በመድረኩ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ፣ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።
በመሳፍንት ብርሌ እና ሶስና አለማየሁ