ፍሰሐ እሸቱ (ዶ/ር ) የተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ክስ እንዲቋረጥ የተሰጠው ብይን ተሻረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፐርTዝ ብላክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሐ እሸቱ (ዶ/ር) የተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ክስ በሌሉበት መታየት አይቻልም ተብሎ ክሱ እንዲቋረጥ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ይግባኝ ሰሚ ወንጀል ችሎት ተሻረ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የፐርTዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ/ማ የቦርድ አባልና ዋና ስራ አስፈጻሚ እነ ፍሰሐ እሸቱ (ዶ/ር) ጨምሮ በ10 ግለሰቦች ላይ እና በሁለት ድርጅቶች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል ተደራራቢ ክስ አቅርቦባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
ዐቃቤ ሕግ በአዲስ አበባ ከተማ 100 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ባለ 3 መኝታ ቤት መኖሪያ ቤት በ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚሸጥ መሆኑን በሚዲያ በማስተዋወቅ ሰዎች ቤት ለመግዛት በሄዱበት ጊዜ ላይ “መጀመሪያ ገንዘቡን አስገቡና ውሉን ትመለከታላችሁ” በማለት ከሌሎች ግብረዓበሮቻቸው ጋር በመሆን አሳሳች ቃላቶችን በመጠቀም፣ ሰዎች ገንዘቡን ካስገቡ በኋላ ደግሞ የአክሲዮን ግዢ ውል እንዲፈርሙ በማድረግ ምንም አይነት የግንባታ ቦታ ባልተረከቡበት ሁኔታ 2 ቢሊየን 234 ሚሊየን 200 ሺህ ብር በመሰብሰብ ቤቱን ሰርተው ሳያስረክቡ በመቅረት እንዲሁም ግማሹን ገንዘብ ወደ ውጭ እንዲሸሽ በማድረግ፣ ኮሚሽን በመቀበልና በማታለል የወንጀል ድርጊት ተፈጽሟል በሚል ነበር ክስ ያቀረበው።
ክስ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል ተራ ቁጥር 1 ላይ የተጠቀሱት ፍሰሃ እሸቱ (ዶ/ር) በቀረበባቸው ስድስት ተደራራቢ ክስ መሰረት በተደጋጋሚ ችሎት ያልቀረቡ መሆኑን ተከትሎ የስር ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸው በሌሉበት መታየት አይችልም በማለት ክሱ እንዲቋረጥ ብይን ሰጥቶ ነበር።
በስር ፍርድ ቤት በአብላጫ ድምጽ የተሰጠው ብይን አግባብ አደለም በማለት ዐቃቤ ሕግ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብሏል
ችሎቱ የዐቃቤ ሕግ ይግባኝ እና የመልስ ሰጪ የስር ፍርድ ቤቱን ብይን መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።
በዚህም የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 161 ንዑስ ቁጥር 2 (ሀ) ሊተረጎም የሚገባዉ በክሱ የተጠቀሰው ድንጋጌ ላይ የተመላከተዉ ቅጣት ወደ 12 አመት ጽኑ እስራት የሚቀርበዉ መነሻ ቅጣቱ ነዉ ወይስ መድረሻ (ጣሪያ) ቅጣት ነዉ የሚለዉ እየተመዘነ መሆን እንዳለበት በስ/መ/ቁ 231732 ከተሰጠዉ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ይዘት ለመገንዘብ የሚቻል መሆኑን ጠቅሷል።
ፍስሐ እሸቱ (ዶ/ር) የተከሰሱባቸዉ ክሶች ከ5ኛ ክስ ዉጪ ያሉት ወንጀሎች የሚያስቀጡት ከ12 አመት እና ከዛ በላይ የመሆን እድላቸዉ ከፍተኛ በመሆኑ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸዉ ሳይቀርቡ ከቀሩ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 161 ንዑስ ቁጥር 2 (ሀ) መሠረት በሌሉበት ክሱ እንዲታይ ማድረግ ሲገባ የስር ፍ/ቤት ክሱ እንዲቋረጥ ማድረጉ ህጋዊ መሠረት የሌለዉ ነው በማለት የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን ሽሮታል።
በዚህም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በታሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ፍሰሀ እሸቱ (ዶ/ር) የተከሰሱባቸዉ የወንጀል ክሶችን በሌሉበት የሚታይ አይደለም በማለት ክሱ እንዲቋረጥ የሰጠዉ ብይን የተሻረ መሆኑን በመረዳት ክሱን መስማት እንዲቀጥል ይፃፍ በማለት ችሎቱ ውሳኔ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ