የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ እና ነገ የሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው ለመሳተፍ የአፍሪካ ሀገሮች መሪዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።
ጉባኤው በተለያዩ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የማካካሻ ፍትህ፣ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ለማግኘት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች፣ አህጉራዊ ሰላምና ደህንነት አጀንዳዎች ውይይት እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አፈጻጸምና አህጉራዊ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር፣ ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ ስርዓተ ጾታና ወጣቶችን ማብቃት እንዲሁም የተቋማት አደረጃጀቶች ላይ ጉባኤው ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።
የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም የተካሄደው 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ መሪዎቹ የሚወያዩባቸውን አጀንዳዎች ማጽደቁ ይታወሳል።