የመደመር ፍልስፍና ፓን አፍሪካኒዝምን ለማጠናከርም ያግዛል- ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር ፍልስፍና ብዝኃነትን እና ህብረትን ለማጠናከር ቁልፍ ሚና እንዳለው ሁሉ ፓን አፍሪካኒዝምንም ለማጠናከር ያግዛል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
38ኛው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባዔ “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቅኝ ግዛት የመጣብንን ጠባሳ ራስን በመቻል እና ድህነትን በማሸነፍ ማሻር ይገባናል ብለዋል።
ለዚህም የተለያዩ ዘመናዊ የግብርና ትልሞችን ተግባራዊ በማድረግ፣ በምግብ ራስን መቻል እና ድህነትን ማሸነፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የተለያዩ ዘመኑን የዋጁ የግብርና ትልሞችን በመጠቀም ከአፍሪካ አንደኛ ስንዴ አምራች ሀገር መሆን መቻሏንም አንስተዋል።
ለቀጣዩ ትውልድም ዘመን ተሻጋሪ መሰረት ለመጣል አፍሪካዊ ዳያስፓራውን ማነቃቃት እና ማሳተፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ በጋራ በመደመር አፍሪካውያን የምንፈልጋትን የበለጸገች አህጉር መፍጠር እንችላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቅኝ ግዛት ጠባሳችን በዚህ ነው የሚድነው ብለዋል።
የአፍሪካ የካሳ ጥያቄ ከቃል ባለፈ ፍትህ የማስፈን ጥያቄ መሆኑን ገልጸው፤ ማንኛውም የሰው ዘር በእኩልነት ተከብሮ ይኖር ዘንድ ፍትህ ማስፈን ወሳኝ ነው ብለዋል።
በሔለን ታደሰ እና መሳፍንት ብርሌ