ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎችን እያመረተ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎች እየተመረቱ እንደሆነ የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ገለጹ፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው በማህበራ ትስስር ገጻቸው÷ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በአዳማ ግብርና መሣሪያዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪ የሚመረተው “ዋይ ቲ ኦ” ትራክተር ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ እንደገና ተመርቶ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል፡፡
“ዋይ ቲ ኦ” ትራክተር በኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና በግብርና መስክ በተሠማሩ ባለሀብቶች ዘንድ የታወቀና የተወደደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ትራክተሮቹ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የተመረቱና ጥራትና ጥንካሬ እንዲኖራቸው ተደርገው የተሻሻሉ ናቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ መንግሥት የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎችን እያመረተ እንደሚያቀርብ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።