ኢትዮጵያ የኅብረቱን ጉባኤ በተሳካ መልኩ እያስተናገደች ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን በተሳካ መልኩ እያስተናገደች መሆኗን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ በ46ኛው የአፍሪካ ኅብረት የስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎችን በክብር ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑንም ተናግረዋል።
በኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መጎልበትን ጨምሮ ለአፍሪካ ኅብረት መጠናከር ጉልህ ሚና ማበርከቷንና ይህንን አጠናክራ እንደምትቀጥል ማንሳታቸውን ገልጸዋል።
በተለይ እርስ በእርስ የተባበረና በመሰረተ ልማት የተሳሰረ አህጉር ለመፍጠር ከሌሎች ውንድም እና እህት አፍሪካውያን ጋር እንደምትሰራ መናገራቸውን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ውጤት ለአፍሪካውያን ምሳሌ እንደሚሆን መግለጻቸውንም እንዲሁ።