በአፍሪካ የወባ በሽታን ለማጥፋት 5 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ የወባ በሽታን ለማጥፋት 5 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በየዓመቱ እንደሚያስፈልግ የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ገለጹ፡፡
በአፍሪካ የወባ በሽታን ታሪክ መቀየር በሚል ከ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ንግግር ያደረጉት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የወባ በሽታን ለማጥፋት በዓመት 5 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል፣ የመድሃኒት አቅርቦት ለማሳደግና ሌሎች ሥራዎችን ለመስራት የገንዘብ አቅርቦት ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
በአፍሪካ በወባ በሽታ በሚሊየን የሚቆጠሩ ህፃናት ህይወታቸውን እንደሚያጡ የሚታወቅ ሲሆን፥ የሚሊየኖችን ህይወት ለመታደግ የወባ በሽታን ማጥፋት ላይ መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል።
ከወባ የፀዳች አፍሪካን እውን ለማድረግ መሪዎች በቅርበት ሊሰሩ ይገባልም ተብሏል።
በአጀንዳ 2063 የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የወባ በሽታን ማጥፋት ላይ መስራት እንደሚገባም ነው የተመላከተው።
በታሪኩ ለገሰ