Fana: At a Speed of Life!

ማዳጋስካር ከኢትዮጵያ መልካም ተሞክሮዎችን በመጋራት በትብብር እንደምትሰራ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከማዳጋስካር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራሳታ ራፋራቫቪታፊካ ጋር ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና ባለብዙ ወገን የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደመከሩም ነው የተገለጸው፡፡

ሚኒስትሮቹ በአጀንዳ 2063፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንት፣ አቪዬሽን፣ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ፣ የቅርስ አያያዝ፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረትን በመጠበቅ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ጌዲዮን (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፥ ኢትዮጵያ እና ማዳጋስካር በቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች የልምድ ልውውጥ ለማድረግና በጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽኖች እና የፖለቲካ ምክክር አህጉራዊ ውህደት ላይ ተባብረው መስራት እንደሚችሉም ነው የተናገሩት።

ራፋራቫቪታፊካ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት ላደረገላቸው ደማቅ አቀባበል እና ታላቅ መስተንግዶ አመስግነዋል፡፡

ሀገራቸው በኢትዮጵያ መልካም ተሞክሮዎችን እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ባሉ የቅርስ አያያዝ፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ የአቪዬሽን ዘርፍ፣ የብዝሀ ህይወት ጥበቃ እና የአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የአየር ንብረት ተሞክሮዎቿን በመጋራት ይበልጥ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.