Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን ለማካሄድ ማቀዷን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በአፍሪካ ሕብረት ለማካሄድ ዕቅድ እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ፡፡

ከ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ኮሚቴ ስብሰባ በኮሚቴው አስተባባሪ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ሰብሳቢነት ተካሂዷል።

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ አፍሪካ እና የተቀረው በማደግ ላይ ያለው የዓለም ክፍል የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቋቋም ልዩ ትኩረት ያሻቸዋል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ አፋጣኝ መፍትሔ የሚያሻው ፈጠራ የታከለበት የፋይናንስ ግኝች ዘዴዎችን መከተል እንደፈልግ ጠቁመው፤ ቃል በተገባው መሰረት ከበለጸጉ ሀገራት በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ አክለውም ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በአፍሪካ ሕብረት ለማካሄድ ዕቅድ እንዳላት መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ጉባዔው ለአሕጉሪቱ ዘላቂ ብልጽግና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ረገድ ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት እና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲመጣ ከኮሚቴው ጋር በትብብር መሥራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.