ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ቱሪዝምን የማስተዋወቅ ሥራ ስኬታማ እንደነበር ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ቱሪዝምን የማስተዋወቅ ሥራ ስኬታማ እንደነበር ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የማይስ ቱሪዝም ማርኬቲንግ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታሪኩ ጉዲሳ እንዳሉት፤ ከየካቲት 5 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደው 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈፃሚዎች እና 38ተኛው የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብቶች የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት ተከናውኗል።
በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲካሄድ የነበረው የማስተዋወቅ ስራ እንደ ሀገር በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ የልማት ስራዎች ከማስተዋወቅ ባሻገር የኢትዮጵያን ምድረ-ቀደምትነት ያስተዋወቀ እንደሆነም አንስተዋል።
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተገኙበት የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት የቡና ስርዓትን ጨምሮ ሌሎች መስህቦችን የማስተዋወቅ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።