ኢትዮጵያ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ጉልህ ሚና እየተጫዎተች መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኡትዮጵያ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍንና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሻሻል ጉልህ ሚና እየተጫወተች መሆኗን በሱዳን የጸጥታ ሁኔታ የሚመክር የአፍሪካ ከፍተኛ የምክክር መድረክ ሊቀ መንበር መሐመድ ኢብን ቻምባሽ (ዶ/ር) ገለጹ።
መሐመድ ኢብን ቻምባሽ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሱዳን ያለውን ጦርነት በራሳቸው በሱዳን ሕዝብ እንዲፈታ እያበረከተች የምትገኘው ያላሳለሰ ጥረት የሚደነቅ ነው።
በጦርነቱ ምክንያት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የምታቀርበው ሰብዓዊ ድጋፍም ለሱዳናዊያን ያላትን ክብር የሚገልጽ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ የሱዳን ስደተኞችን እየተቀበለች መሆኑን መጠቀሱን ገልጸው፤ ይህም ተግባር የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ 46ኛው የስራ አስፈጻሚ ጉባኤ ላይ በተደረገው ውይይት በሱዳን ያለው ጦርነት መቆም እንዳለበት ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
በጦርነቱ በርካታ መሠረተ ልማቶች መውደሙንም ጠቁመው፤ አሁን በሚመጣው የረመዳን ጾም ጦርነቱ እንደሚቆም ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተኩስ አቁም ስምምነት ወሳኝ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የተኩስ አቁሙ እንዲተገበር እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ የሚመክረው የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ አፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ አዘጋጅነት ሰሞኑን በተካሄደበት ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝብ ሰላምና መረጋጋት በሁሉም መስክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች።
ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የሚውል 15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግም ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።