ሊቨርፑል መሪነቱን የሚያጠናክር ድል አስመዘገበ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር አንፊልድ ላይ ዎልቭስን ያስተናገደው ሊቨርፐል 2 ለ 1 በማሸነፍ ነጥቡን 60 በማድረስ መሪነቱን አጠናክሯል።
ሊቨርፑል በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ባደረገው በዚህ ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ያሰፋበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
በሉዊስ ዲያዝ እና ሞሃመድ ሳላህ ግቦች 2 ለ 0 እየተመሩ የመጀመሪያውን አጋማሽ የጨረሱት ዎልቭሶች ከእረፍት መልስ ተጭነው በመጫወት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጠንካራ ፍልሚያ አድርገዋል።
ጠንካራ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ የዎልቭስን የማስተዛዘኛ ግብ ማቲያስ ኩንሃ አስቆጥሯል።
ሊጉን ሊቨርፐል በ60 ነጥብ ሲመራ አርሰናል በ53 ነጥብ እየተከተለ ይገኛል።
ኖቲንግሃም ፎረስት 47 እንዲሁም ማንቼስተር ሲቲ 44 ነጥብ በመሰብሰብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሶስተኛ እና አራተኛ ላይ ተቀምጠዋል።