የአሜሪካ ባለስልጣናት ከሩሲያ ጋር ለሚደረገው ንግግር ወደ ሳዑዲ ሊያቀኑ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ከሩሲያ ጋር በሳዑዲ አረቢያ በሚደረገው ንግግር ላይ ለመሳተፍ ከብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ማይክ ዋልትዝ ጋር እንደሚጓዙ አስታወቁ።
የአሜሪካ እና ሩሲያ ባለስልጣናት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ያለመ ንግግር ለመጀመር በሳዑዲ አረቢያ ሊገናኙ መሆናቸውን ሲዘገብ ቆይቷል።
በዚህም የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ ወደ ሳዑዲ እንደሚጓዙ ለፎክስ ኒውስ መናገራቸው የመጀመሪያ ኦፊሴላዊ ማረጋገጫ ሆኗል።
በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መመሪያ መሰረት ስብሰባውን እናደርጋለን ሲሉ የገለጹት ስቲቭ ዊትኮፍ የተሻሉ ሂደቶችን እንደምንፈጥርም ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ግን ሀገራቸው በዚህ በሳዑዲ አረቢያ በሚደረገው የአሜሪካ እና ሩሲያ ንግግር ላይ እንድትገኝ እንዳልተጋበዘች ተናግረዋል።
አክለውም ዩክሬን ከአውሮፓ አጋሮቿ ጋር ሳትመክር ከሩሲያ ጋር እንደማትገናኝ ገልጸዋል።
የአውሮፓዊቷ ሀገር የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚህ በዶናልድ ትራምፕ ድርጊት ዙሪያ ለመወያየት የአውሮፓ መሪዎችን ለአስቸካይ ስብሰባ መጥራታቸው ታውቋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አጋሮቻቸውን ወደ ጎን እየተው ነው የሚለው ስጋት በአስቸኳይ ለተጠራው ስብሰባ ምክንያት እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ትራምፕ በሩሲያ ዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት ማስቆም የሚያስችል ድርድር በፍጥነት እንዲጀመር ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደተስማሙ በገለጹበት ወቅት ቡድኖች ተዋቅረው በአስቸኳይ ድርድር ይጀመራል ማለታቸው ይታወሳል።