ፍትህ ሚኒስቴር የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በዲጂታል መታወቂያ ብቻ ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በዲጂታል መታወቂያ ብቻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በፍትህ ሚኒስቴር እና በተጠሪ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በብሔራዊ መታወቂያ ብቻ ማድረግ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ለጠበቆች የመታወቂያ መስጠት እና ማደስ አገልግሎትን በዲጅታል መታወቂያ ብቻ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ሰነዳቸውን ሙሉ በሙሉ ዲጅታላይዝ የማድረግ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ይህንንም ከዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በማስተሳሰር አገልግሎት እንደሚጀምር ጠቅሰው፤ በብሔራዊ መታወቂያ ብቻ የሚሰጡ አገልግሎቶችን የመለየት ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
በመሳፍንት እያዩ